የፍቅር ጥግ

ሰማይ ሙሉ ዙፋን -መሬት መረገጫ፣

ዓለም ሁሉ የሱ-መንገሻ ማጌጫ።

የፍጥረታት ገዢ- የአማልክት አምላክ፣

ሥልጣን ሐያልነት-የሌለው መጠን ልክ።

ሁሉ በእጁ ሳለ-ሁሉም በሱ ደጅ፣

ተገኘ በግርግም-ሆኖ ህጻን ልጅ፣

ታቀፈ ከድንግል-ዓለምን ሊዋጅ።

የፍቅሩ ስፋት ልክ-የመውደዱ ብዛት፣

ሚዛን፣መለክያ፣መጠን፣ወሰንም...የለበት፣

አስተኛው ከግርግም-አደረሰው ከሞት።

ካለ ቤተ መንግስት-ካለ ወርቁ አልማዝ፣

ካልጠፋ የሚላክ-እያለ ሚመዘዝ፣

ካልጠፉ ሎሌዎች-ሞልቶ የሚታዘዝ።

አምላከ አማልክት-እግዚኧ አጋእዝት፣

መሬት ወርዶ ታዬ-ሲሰቃይ ሲዋትት፣

አደረ ከድንግል-ለካው ጠባብ ደረት፣

ከኛ ጋር ማሰነ-ተወሰነ በቁመት፣

የፍቅሩ ስፋት ልክ-የመውደዱ ብዛት፣

ሚዛን፣መለክያ፣መጠን፣ወሰንም...የለበት፣

አስተኛው ከግርግም-አደረሰው ከሞት።

እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሰን ፣አደረሳሽሁ!!!

ቅዳሜ ታሕሣሥ 29 2009 ዓ.ም.

ኤድመንተን ካናዳ